ከተማውን ለኑሮ እና ስራ ምቹ በማድረግ አበረታች ውጤት ተመዝግቧል-ርዕሰ መስተዳር አቶ ኦርዲን በድሪ

ባለፉት ስድስት ወራት የሐረር ከተማን ለኑሮና ስራ የተመቸች በማድረግ አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ርዕሰ መስተዳር አቶ ኦርዲን በድሪ አስታወቁ።

በሐረሪ ክልል ባለፉት 6 ወራት የተከናወነው የኮሪደር ልማት ስራ ለኑሮ እና ስራ የተመቸች ከተማን በመፍጠር አበረታች ውጤት የታየበት መሆኑን ርዕሰ መስተዳር አቶ ኦርዲን በድሪ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት የ 6 ወራት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ገልፀዋል።

የሐረር ከተማን ፅዱ፤ውብ እና አረንጓዴ ለማድረግ የተከናወኑ አበረታች ተግባራትም የከተማዋን የቀድሞ ገፅታ የቀየሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።

በተለይ በኮሪደር ልማት እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት የሐረር ከተማን ለኑሮና ስራ የተመቸች በማድረግ አበረታች ለውጦች የታዩበት መሆኑን አክለዋል

የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድን በማሳለጥ፤አረንጓዴ እና መናፈሻ ስፍራዎችን በማስፋት ከተማዋን ለነዋሪዎቿ እና ለጎብኚዎች አረንጓዴ ውብና ጽዱ ማድረግ ተችሏል።

በቀን ሶስት ጊዜ የደረቅ ቆሻሻን በማንሳት ከተማዋን ጽዱ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራትም ከተማውን ፅዱ እንዲሆን አስችለዋል።

በተለይ ደረቅ ቆሻሻን መልሶ ከመጠቀም አኳያ በማህበር የተደራጁ ወጣቶችና ሴቶችን ወደ ስራ በማስገባት ደረቅ ቆሻሻን በአግባቡ በማስወገድ የከተማዋን ንጽህና የመጠበቅ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

በዚህም በዘርፉ ለተሰማሩ ስድስት ማህበራትና እና 8 መቶ ለሚሆኑ ሴቶች የስራ እድል መፈጠሩን ጠቅሰዋል።

በከተማው የአረንጓዴ ስፍራዎችና መናፈሻዎችን ከማስፋት አንጻርም የተለያዩ ግለሰቦችን ባሳተፈ መልኩ የአረንጓዴ ልማት ና መናፈሻዎች ስራ መከናወናቸውን ተናግረዋል።

ከተማዋን ውብ ከማድረግ አንጻርም ከዚህ ቀደም አገልግሎት አቋርጠው የነበሩ ከአንድ ኪሎ ሜትር በላይ የመንገድ ዳር መብራቶች ተጠግነው ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉን ገልጸዋል።

በከተማው የሚታየውን ህገ ወጥነት ከመከላከል አንጻርም ባለፉት 6 ወራት በጎዳና እና መንገድ ዳር ግብይት የሚፈጽሙ 2 ሺህ 2 መቶ 61 ህገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ በመውሰድ መንገዶችን ለእግረኛና ተሽከርካሪዎች ክፍት እንዲሆኑ የማድረግ ስራ መከናወኑን ገልጸዋል።

በከተማው በህገ ወጥ መንገድ ተወሮ የነበረ 2 ነጥብ 6 ሄክታር መሬት ወደ መንግስት እንዲመለስ መደረጉንም አክለዋል።

በቀጣይም ከተማዋን ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያሸጋግሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገልፀዋል።

+5

All reactions:

Scroll to Top