በሐረሪ ክልል የትምህርት ጥራት እና ተደራሽነትን በማረጋገጥ አበረታች ውጤቶች ማስመዝገብ መቻሉን ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ አስታወቁ።
ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ እየተካሄደ በሚገኘው የክልሉ ምክር ቤት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት 7ኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ ባቀረቡት ሪፖርት እንደገለፁት ባለፉት ስድስት ወራት በትምህርት ጥራት እና ተደራሽነት አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል።
በበጀት ዓመቱ የትምህርት ዘርፉን ስብራቶች በመለየት ለትምህርት ጥራት እና ተደራሽነት ልዩ ትኩረት በመስጠት ወደ ስራ መገባቱን ገልፀዋል።
በክልሉ የትምህርት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በተሰራው ስራም በሁሉም የከተማ እና የገጠር ወረዳዎች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ብሎም በቀበሌዎች እና መንደሮች የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት የትምህርት ተደራሽነትን ማረጋገጥ መቻሉን ገልፀዋል።
ባለፉት 6 ወራት አዳዲስ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ማስፋፊያ ፕሮጀክቶቸ ተመርቀው ለአገልግሎት መብቃታቸውንም ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል በክልሉ የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ የተማሪ ውጤትን ለማሻሻል ከቅድመ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጀምሮ ትኩረት መሰጠቱን በሪፖርቱ ጠቁመዋል።
በዚህም ተማሪዎች በአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸው በቂ እውቀት ቀስመው የስሌት፤የማንበብ እና አንብቦ የመረዳት ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ ለማስቻል ልዩ ትኩረት ተሰቶ እየተሰራ ነው።
በተለይ በ2016 በ6ተኛ፤8ተኛ እና 12ተኛ ክፍል የተመዘገበውን የተማሪ ውጤት ለማሻሻል ከተማሪ ወላጆች፤ መምህራን እና የትምህርት አመራሮች ጋር ውይይት በማድረግ ልዩ ትኩረት በመስጠት እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
የትምህርት ሰአት ብክነት በትምህርት ዘርፉ በስብራት ከተለዩ ምክንያቶች አንዱ መሆኑን በመጠቆም ትምህርት ቤቶችን ሪፎርም በማድረግ፤ የቁጥጥር ስርዓቶችን በመዘርጋት ባለሞያ መድቦ በትምህርት ቤቶች ላይ የክትትል እና ቁጥጥር ስራ ሲከናወን መቆየቱን ገልፀዋል።
ይህም በትምህርት ቤቶች ቀድሞ ይስተዋል የነበረውን የትምህርት ሰዓት ብክነት በማስቀረት በአንደኛው ወሰነ ትምህርት በተሰጠው ፈተና ውጤት ትንተና መሰረት የተማሪ ውጤት መሻሻል ማሳየቱን አስታውቀዋል።
የተማሪ የማለፍ ምጣኔን ለማሳደግም በትምህርት ቤቶች ቅዳሜን ጨምሮ የማጠናከሪያ ትምህርቶችን ከመስጠት ባሻገር ሞዴል ፈተናዎችን ለተማሪዎች በመስጠት ለቀጣይ ክልላዊ እና አገር አቀፍ ፈተናዎች የማዘጋጀት ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ አክለዋል።
በሌላ በኩል በክልሉ መንግስት በተመደበ በጀት ከ 38 ሺ በላይ ተማሪዎችን ያቀፈ የትምህርት ቤት ምገባ ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
የትምህርት ቤት ምገባው ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው ላይ እንዲቆዩ በማድረግ መጠነ ማቋረጥ እንዲቀንስ ከማስቻሉም ባሻገር
የተማሪዎች የትምህርት ቅበላን በማዳበር በተጨባጭ ውጤት የተመዘገበበት ነው።
በመርሀ ግብሩ ከ6 መቶ በላይ ለሚሆኑ የተማሪ ወላጆች የስራ ዕድል በመፍጠር የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ መቻሉንም ጠቁመዋል።
በክልሉ ለልዩ ፍላጎት ተማሪዎች ትኩረት በመስጠት 3 ሺ 989 ልዩ ድጋፍ የሚሹ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ዕድል መመቻቸቱንም ርዕሰ መስተዳድሩ አስረድተዋል።
በሌላ በኩል በክልሉ በ 78 ማስተባበሪያ ጣቢያዎች ከ 2ሺ 600 በላይ ጎልማሶች የቀለም ትምህርት እንዲከታተሉ ተደርጓል ብለዋል።
የተማሪ የመማሪያ መፅሀፍ ስርጭት ምጣኔን በተመለከተም በዋና ዋና ትምህርቶች 1 መፅሀፍ ለአንድ ተማሪ ማድረስ ተችሏል።
የትምህርት ቤቶች ደህንነት ለማረጋገጥ በተሰራው ስራ በትምህርት ቤቶች አቅራቢያ ተከፈተው የነበሩ መጠጥ ቤቶች፤ጫት ቤቶች እና ሌሎች ያልተገቡ ተቋማት ላይ እርምጃ በመውሰድ የማጥራት ስራ መሰራቱን በሪፖርቱ አብራርተዋል።