የኢትዮጲያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ብሔር ብሔረሰቦች እሴቶቻአቸውን የሚያጋሩበት እንዲሁም ህብረ ብሄራዊ አንድነታቸውን የሚያፀኑበት መሆኑ ተገለፀ።

በየዓመቱ ህዳር 29 የሚከበረው የኢትዮጲያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ዘንድሮ ለ19ኛ ጊዜ “ሀገራዊ መግባባት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል በድሬዳዋ አስተዳደር በተለያዩ ሁነቶች ሲከበር ቆይቷል በዛሬው እለት የማጠቃለያው መርሀ-ግብር ተከናውኗል፡፡
በማጠቃለያው መድረክም የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ክብርት ወ/ሮ ፈቲያ አደን፣ የብልፅግና ፓርቲ የድሬዳዋ ቅ/ፅ ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ይሱፍ፣ የክልልና የአዲስ አበባ አስተዳደር አፈ-ጉባኤዎችና ም/አፈ-ጉባኤዎች፣ የካቢኔ አባላት፣ በአስተዳደሩ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች፣ የሀይማኖች አባቶች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል፡፡
በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ክብርት ወ/ሮ ፈቲያ አደን ለእንግዶች የእንኳን ደና መጣችሁ መልዕክታቸውን በማስተላለፍ በዓሉ የኢትዮጲያ ብሄር ብሄረሰቦች እሴቶቻአቸውን የሚያጋሩበት እንዲሁም ህብረ ብሄራዊ አንድነታቸውን የሚያፀኑበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የዘንድሮ በዓል የህልም ጉልበታችንን ለእምርታዊ እድገት እውን ለማድረግ የጋራ እሴቶቻችንን አዳብረን በቁርጠኝነት ስሜት የሁለንተናዊ ብልፅግና ጉዞአቸችንን ከዳር ለማድረስ በሁሉም አቅጣጫ ተስፋ ሰጪ ደረጃ ላይ በደረስንበት ወቅት መከበሩ በዓሉን ልዩ ያደርገዋል ሲሉም ክብርት ወ/ሮ ፈቲያ ተናግረዋል፡፡
ለዘመናት የቆየውና አሁንም ጎልቶ የሚታየው የአስተዳደራችን የሰፈነ ሰላምና ፀጥታ ሚስጥር አንድነታችንና መቻቻላችን ነው ሲሉ የተናገሩት አፈ-ጉባኤዋ አንድነት ተመሳሳይነት አይደለም፤ አንድነት የተለያዩ ሰዎች ለአንድ አላማ መስራት ነው ሲሉም አብራርተዋል፡፡
በመጨረሻም በአሉን ስናከብር ህብረ ብሄራዊ የፌደራል ስርአታችን እያጋጠሙት ያሉትን ተግዳሮቶች አንስተን ከአካባቢያችን ነባራዊ ሁኔታዎች ጋር እያዛመድን መወያየትና ተግዳሮቶችን ለመሻገር የሚያስችሉ እርምጃዎችን በመውሰድ ህብረ ብሄራዊ የፌደራል ስርአታችን የበለጠ የሚጎላበትን አቅጣጫ በመከተልም ነው ሲሉ ክብርት ወ/ሮ ፈቲያ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
Scroll to Top