በክልሉ 19ኛው የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ቀን በተለያዩ ኩነቶች እየተከበረ እንደሚገኝ የሐረሪ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ- ጉባኤ አቶ አሪፍ መሀመድ ገልጸዋል።
ምክትል አፈጉባኤው በአሉን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ እንዳሉት በየአመቱ ህዳር 29 የሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦች በዓል የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች አንድነትን እኩልነትንና የፌደራል ስርዓቱን ከማጠናከር አንፃር ጉልህ ድርሻ አለው፡፡
ዘንድሮ ለ19ኛ ጊዜ “ሀገራዊ መግባባት ለኅብረብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል የሚከበረው በዓልም በክልሉ በተለያዩ ኩነቶች እየተከበረ ይገኛል ብለዋል።
በክልል ደረጃ በአሉ የሚመራበት መሪ እቅድ ተዘጋጅቶ እና ኮሚቴዎችን ተቋቁመው የበዓሉ አከባበር የተሳካ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውን ጠቁመዋል።
በዓሉ በተለይም በህዝቦች መካከል ያለውን አንድነትና እኩልነት በሚያጠናክርና ህብረ ብሄራዊነትና የፌዴራል ስርዓቱን በሚያጎለብት መልኩ እየተከበረ መሆኑን አብራርተዋል።
በዚህም በፌዴራሊዝም ጽንሰ ሀሳብ ዙሪያ በፓናል ውይይቶች፣ የጥያቄና መልስ ውድድሮች፣ ስፖርታዊ ውድድሮች፣ የሙዚየም ጉብኝቶች፣ በጽዳት ዘመቻ ሰብል በመሰብሰብና በሌሎች መርሃግብሮች እየተከበረ ስለመሆኑ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ቀን በአመት አንድ ግዜ የምናከብረው በአል ብቻ ሳይሆን ሁልጊዜም በአካባቢያችን በመቻቻል፣ በመከባበርና ግንኙነታችንን በማጠናከር ማክበርም እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡
19ኛው የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ቀን በክልል ደረጃ ህዳር 23 /2017 ፍጻሜውን እንደሚያገኝም ምክትል አፈ- ጉባኤው አስገንዝበዋል፡፡
18 / 03 / 2017
