ከለውጡ ወዲህ ፌደራላዊ ሥርዓቱን በመተግበር ተጨባጭ ለውጦች ተመዝግበዋል – ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ

ከለውጡ ወዲህ ህገ መንግስቱን ወደ ተጨባጭ እውነታዎች በመቀየር ህብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጎልበት አበረታች ለውጦች ማስመዝገብ መቻሉን የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለፁ።
በሀረሪ ክልል19ኛው የብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በዓል ማጠቃለያ መርሀ ግብር ተካሂዷል።
የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በማጠቃለያ መርሀ ግብሩ ላይ ከለውጡ ወዲህ ህገ መንግስቱን ወደ ተጨባጭ እውነታዎች መቀየር መቻሉን ገልፀዋል።
በተለይ የፌዴራሊዝም ስርዓቱ ተግባራዊ እንዲሆን በማስቻል ህብረብሔራዊ አንድነትን በማጎልበት አበረታች ለውጦች ማስመዝገብ መቻሉን አክለዋል።
ህገ መንግስቱ የሁሉም ኢትዮጵያ ዜጎች ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚዊ እና ማህበራዊ መብቶች እና ነፃነቶች ህገ መንግስታዊ ዋስትና እንዲኖረው አስችሏል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመለክታል።
ከህገ መንግስቱ የመነጨው ህብረብሔራዊ ፌደራላዊው ሥርዓት ለሁሉም ማንነቶች እኩል ዕውቅና በመስጠት፣ የአካባቢያቸውን የመልማት አቅም እና ፍላጎት መሠረት በማድረግ እንዲለሙ እድል መፍጠሩንም ገልፀዋል።
በተለይ ቋንቋቸውን፣ ባህላቸውን እና ታሪካቸውን የሚገልጹበት የፓለቲካ ምህዳርን በማስፋት፣ የራሳቸውን ጉዳይ በራሳቸው የሚያስተዳድሩበት የወል ምህዳር በማመቻቸት፣አገራዊ እና የጋራ በሆኑ ጉዳዮች ላይ እኩል ተሳታፊ እንዲሆኑ ማስቻሉን ነው ያነሱት።
ህብረ ብሄራዊ ወንድማማችነትን ለማጠናከር በተሰራው ስራ አመርቂ ውጤቶችን መጎናጸፍ ቢቻልም የፌደራል ሥርዓቱ እና ህገ መንግስታዊነት ባለመዳበሩ ተግዳሮቶች መስተዋላቸውን ጠቅሰዋል።
እነዚህን ተግዳሮቶች በውይይት ለመቅረፍ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በማቋቋም ተሳታፊዎችን እና የምክክር አጀንዳዎችን የመለየት ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
19ኛው የብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በዓል ሀገራዊ ምክክር በጀመርንበት ግዜ የሚከበር መሆኑ ዕለቱን ለየት እንደሚያደርገውም ጠቁመዋል።

Scroll to Top